አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ፈሰስ ተደርጎበት ለሚገነባ ኩባንያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የመሰረት ድንጋይ አስቀመጠ።
የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሚል ኢብራሂም፣ የኮርፖሬት ሀብት አስተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አለማየሁ ሰይፉ እና የፔሪ ሜትር ኮንሰልቲንግ ማኔጅንግ ዳይሬክተር ቤተልሄም ጥላሁን የመሰረተ ድንጋዩን አስቀምጠዋል።
የሚገነባው ማምረቻ ከጤፍ የተለያዩ ስናኮችንና ደረቅ የምግብ ዓይነቶችን የሚያመርት ሲሆን በፔሪ ሜትር ኮንሰልቲንግ እና ትሬዲንግ ኩባንያ አማካኝነት ነው የሚገነባው።
በዚሁ ወቅት የኮርፖሬሽኑ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሚል ኢብራሂም÷ ወደ ኮርፖሬሽኑ ለሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ማምረቻውን በ11 ሄክታር የለማ መሬት ላይ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የፔሪ ሜትር ኮንሰልቲንግ ኩባንያ ከ1 ኘጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግበትም የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
የግንባታ ስራው ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ምርቶቹን ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ እና የሩቅ ምስራቅ ሀገራት እንደሚልክ ተገልጿል።