Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የቡድን 7 ሀገራት መሪዎች በጋዛና ዩክሬን ጉዳዮች ለመምከር ተሰበሰቡ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቡድን 7 ሀገራት መሪዎች በሀማስ እና እስራኤል እንዲሁም በዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ላይ ለመወያየት በጣልያን መሰብሰባቸው ተሰምቷል፡፡

ስብሰባው ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን፥ የሠባቱ የበለጸጉ ሀገራት መሪዎች ስለ ሩሲያ – ዩክሬን እና እስራኤል – ሃማስ ጦርነቶች፣ የሃይል አቅርቦት፣ የሰው ሰራሽ አስተውህሎት፣ ፍልሰትን አስመልክተው ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ከካናዳ፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ጃፓን አቻቸው ጋር በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ለመምከር በየዓመቱ ይገናኛሉ።

በዚህ ስብሰባም ፖፕ ፍራንሲስን ጨምሮ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ፣ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይፕ ኤርዶሃን እና ሌሎች መሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ስብሰባውን ይመራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የዘገበው አፍሪካ ኒውስ ነው፡፡

በስብሰባው እጅግ ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል የተያዙ የሩሲያ ንብረቶች ዩክሬንን ለመርዳት እንዲውሉ ሊተላለፍ የሚችለው ውሳኔ እንደሆነም ተጠቁሟል።

Exit mobile version