የሀገር ውስጥ ዜና

ከተረጅነት በመላቀቅ አደጋን መቋቋም የሚያስችል ጠንካራ ሀገራዊ ቁመና ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

By Amele Demsew

June 13, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በለውጡ ዓመታት ከተረጅነት ስነ ልቦና በመውጣት በራስ አቅም አደጋን መቋቋም የሚያስችል ጠንካራ ቁመና ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ እና የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ÷በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተረጅነትና ልመናን ባህል አድርገውት ቀጥለዋል ብለዋል።

በለውጡ ዓመታት ከተረጅነት ስነ ልቦና በመውጣት በራስ አቅም አደጋን መቋቋም የሚያስችል ጠንካራ ቁመና ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር)በበኩላቸው ÷ የኢትዮጵያን ጸጋ በማልማት ጥቅም ላይ ማዋል ባለመቻሉ ተረጅነትና ልመና ልምድ ሆኖ መቀጠሉን ገልጸው ፤ ይህም የብዙዎችን የመፍጠርና የመስራት ባህል እየጎዳ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ብልፅግና ፓርቲ በሁሉም ለሁሉምና የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን መገንባት የሚያስችሉ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።

በለውጡ ዓመታትም የዜጎችን ክብር ለማረጋገጥ ፖሊሲዎቿን በነጻነት የምትተገብር ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ትምህርት የሰጡ የልማት ስኬቶች መመዝገባቸውን ሚኒስትሮቹ ገልጸዋል።

መንግስት ተረጅነትን የማስቀረት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱን ከማሳየት ባለፈ ህዝብን አስተባበሮ ፈጣን ልማትን ለማስቀጠል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች የተረጅነት ባህልን ለመቅረፍ መግባባት፣ ወስኖና አቅዶ መተግባር የሚያስችል ተግባቦት የተፈጠረባቸው ናቸው ብለዋል።