Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ ለማሰራጨት የትራንስፖርት ኦፕሬተሮች በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፈር ማዳበሪያ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም የትራንስፖርት ኦፕሬተሮች በከፍተኛ ቁርጠኝነት እንዲሰሩ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የትራንስፖርት ኦፕሬተር አመራሮችና ባለንብረቶች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ወቅቱን ጠብቆ ስለማጓጓዝ በትኩረት መክረዋል፡፡

በመድረኩ÷ ለ2016/17 የምርት ዘመን ቀሪ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ወቅቱን ጠብቆ መጓጓዝ እንዳለበት ተመላክቷል፡፡

ቀደም ሲል ወደ ሀገር ውስጥ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ የገባ ሲሆን÷ ቀሪው ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ መግባት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡

የአፈር ማዳበሪያ ጉዳይ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም የድንበር ተሻጋሪ ጭነት ትራንስፖርት ኦፕሬተር አመራሮች በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ተጠይቋል፡፡

ከባህር ትራንስፖርት ጋር ውል ያልገቡ የድንበር ተሻጋሪ ጭነት ትራንስፖርት ኦፕሬተር አመራሮችና ባለንብረቶች የአፈር ማዳበሪያ ለማጓጓዝ ውል በመፈፀም እንዲያጓጉዙ ጥሪ መቅረቡንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version