Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የጫካ ፕሮጀክት የኃይል መሰረተ-ልማት ግንባታን እስከ ነሐሴ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጫካ ፕሮጀክት የተጀመረውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፊያ ጣቢያ ግንባታ እስከ ነሐሴ 2016 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

በፕሮጀክቱ ክልል የሚያልፉ የማስተላለፊያ መስመሮችን ከፓርኩ ማስተር ፕላን ጋር በማጣጣም መስመሮችን የማዛወርና በጊዜያዊነት ለኃይል አቅርቦት የሚያገለግል የተንቀሳቃሽ ማከፋፊያ ጣቢያ ተከላ እየተከናወነ መሆኑንም ነው ተቋሙ ያስታወቀው፡፡

የግንባታ ሥራው በጫካ ፓርክ አቋርጦ የሚያልፈውን የኮተቤ – ቤላ ባለ 132 ኪሎ ቮልት ማስተላለፊያ መስመር የማዛወር ሥራ እንደሚያካትት አስታውቋል፡፡

እንዲሁም የ3 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የመሬት ውስጥ፣ የ0 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የአየር ላይ (ኦቨር ሄድ) መስመር ዝርጋታ እና የ0 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮንዳክተር ቅየራ ሥራዎችን እንደሚያጠቃልል ገልጿል፡፡

ከኮተቤ – አያት ከተዘረጋው ባለ 132 ኪሎ ቮልት መስመር ላይ 0 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትሩን በመሬት ውስጥ የመቀየር ሥራ በተጓዳኝ እንደሚከናወን ማሳወቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ የኮተቤ – አዲስ ኢስት ባለ 132 ኪሎ ቮልት ጥምር የማስተላለፊያ መስመርን የማዛወር ሥራ እንደሚከናወን ገልጾ÷ ይህም የ1 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የመሬት ውስጥ እና የ1 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የአየር ላይ መስመር ዝርጋታ ሥራን ያካትታል ብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለኮተቤ – ቤላ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የመስመር ማዛወር ሥራ የሚያስፈልጉ ዕቃዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውንም አረጋግጧል፡፡

ከቤላ እስከ ጫካ ተንቀሳቃሽ ማከፋፊያ ጣቢያ ያለው የ0 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመር የተከላ እና ፍተሻ ሥራ መጠናቀቁንና የተንቀሳቃሽ ማከፋፊያ ጣቢያው የፍተሻ ሥራ መጀመሩንም አስረድቷል፡፡

ለኮተቤ – አዲስ ኢስት መስመር ማዛወር ከሚያስፈልጉ 6 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች የአራቱ የተከላ ሥራ ተጠናቅቆ ኮንዳክተር የመዘርጋት ስራ መጀመሩን ያስታወቀው ተቋሙ÷ ቀሪ ሁለት ምሰሶዎች የከፍተኛ መስመር ኃይል ማቋረጥ ስለሚጠይቁ መሬት ላይ ቀድመው መሰራት ያለባቸው ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብሏል፡፡

የተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያ ሲቪል ስራ እንዲሁም ከኮተቤ ጫካ በነባር ምሰሶዎች ላይ የጥገና እና የማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ስራ እየተከናወነ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

አሁን ባለው የፕሮጀክቱ የሥራ ወሰን መሰረት የመሬት ውስጥ መስመር ዝርጋታ ስራ ላይ የክረምቱ የአየር ሁኔታ ተፅዕኖ የማያሳድር ከሆነ ሥራዎችን እስከ ነሐሴ 2016 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጭ 370 ሚሊየን ብር የሚገመት ሲሆን÷ ሙሉ ወጪው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸፈን ይሆናል፡፡

Exit mobile version