Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያን እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች በማልማት ተመፅዋችነትን ማስቀረት የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ነው – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች በማልማት ተመፅዋችነትን ማስቀረት የሚያስችል ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የበጀት ዓመቱ የመጨረሻው የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ÷የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማው በማክሮ ኢኮኖሚና ዋና ዋና ዘርፎች አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ በበጋ መስኖ፣ በሩዝ ልማትና በአጠቃላይ ሰብል ልማት ከፍተኛ ምርት መገኘቱን ጠቅሰዋል።

በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርም እያንዳንዱ ቤተሰብ የተመጣጠነ የምግብ ሽፋንን እንዲችልና የአመጋገብ ባህሉን እንዲለውጥ የሚያድርግ ምዕራፍ መከፈቱን ነው የተናገሩት።

በምግብ እህል ራስን ለመቻል ኢኒሼቲቮችን ከመተግበር ባለፈ ከህዝቡ ጋር መግባባት በመፍጠር ለልማት ቆርጦ እንዲነሳ በየክልሎች ሰፋፊ መድረኮች መከናወናቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የተመፅዋችነት ታሪክ እንዲያበቃ ከታታሪው ህዝብ ጋር በመሆን ያለውን ለም አፈርና ውሃ ተጠቅሞ ምርታማነትን ለማሳደግ ሌት ተቀን ለመስራት ተነስተናል ነው ያሉት።

በውይይት መድረኮቹም ህዝቡ የልመና ባህልን ለማስቀረት ቁርጠኝነቱን ማሳየቱን ጠቅሰው፥ በ100 ቀናት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረኩ የተቀመጠው አንዱ አቅጣጫም ይኸው እንደሆነ አስረድተዋል።

በሌላ በኩል የአዲስ አበባን ገፅታ የሚቀይሩ፣ ለነዋሪዎቿ ኑሮና ለመዝናኛ የሚመቹ የኮሪደር ልማቶች በተቀናጀ መልኩ በመተግበር ውጤት መምጣቱን አንስተዋል።

ይህንን ተሞክሮ ወደ ክልሎች በማስፋት በአብዛኛዎቹ ከተሞች የኮሪደር ልማት እየተተገበረ እንደሚገኝም መተቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪና በማዕድን ዘርፍ ያለውን ውጤታማነት ለማሳደግ የፋብሪካዎችን አቅም በእጥፍ የማሳደግ ስራ ትኩረት እንዲሰጠው አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል።

ይህም ከአንድ ዓመት በኋላ ከዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ነው ያሉት።

በጥቅሉ በዚህ ዓመት የተተነበየውን የ7 ነጥብ 9 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ማሳካት የሚያስችል አመላካች ውጤት መኖሩን ጠቅሰው÷ በመጪው በጀት ዓመትም ከ8 ነጥብ 3 በመቶ ያላነሰ እድገት እንዲመዘገብ ታቅዷል ብለዋል።

ለዚህም በበጀት ዓመቱ የዝግጅት ምዕራፍ የሚል የጊዜ ሰሌዳን በማስቀረት በአፋጣኝ ወደ ስራ እንዲገባ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።

Exit mobile version