አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የ12ኛክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ከ700 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች በወረቀትና በኦላይን ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና መርሃ-ግብር እና የኦንላይን ፈተና ለመስጠት እየተደረገ ያለውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና በድብልቅ (በወረቀትና በኦንላይን )ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረግ መሆኑን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ተፈራ ፈይሳ ገልጸዋል።
በዚህም ለተፈታኝ ተማሪዎች በወረቀትና በኦላይን ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችል አስፈላጊው የፈተና ዝግጅት፣ ህትመት፣ ተፈታኝ ተማሪዎችን በስነ ልቦና የማዘጋጀትና በየዩኒቨርሲቲው የመመደብ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ተናረዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ዲጅታላይዜሽንና አይሲቲ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዘላለም አሰፋ(ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በኦንላይን ፈተናቸውን የሚወስዱ ተማሪዎችን ቴክኖሎጂውን እንዲያውቁት ፈተናዎች በሶፍትዌሩ ተጭኖላቸው እንዲለማመዱ መደርጉን መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በተለይም የኔትዎርክ እና የመብራት መጠባበቂያ ጀኔሬተር የሌላቸው ተቋማት በፈተና ጣቢያነት እንደማይመረጡ የገለጹ ሲሆን÷ ለዩኒቨርሲቲዎችና ከዩኒቨርሲቲ ውጭ ላሉ ተቋማት በክላስተር በማድረግ በፈተና ወቅት አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርጉ ባለሙያዎች መመደባቸውንም ተናግረዋል።
ፈተናውንም በኦንላይን ለመስጠት በመንግስት በኩል አስፈላጊው የግብዓት ዝግጅት የተደረገ መሆኑን ገልጸው÷ በተለያዩ ሚድያዎች ተማሪዎች ላፕቶፕ ኮምፒዉተር ገዝተው እንዲያመጡ ታዘዋል በሚል የሚነሳው ሃሳብ ሀሰት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና ከሃምሌ 3 ቀን 2016 ጀምሮ እንደሚሰጥ መገለጹ ይታወቃል።