አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማላዊ ምክትል ፕሬዚዳንት ሳውሎስ ቺሊማን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎችን አሳፍሮ ትናንት ተሰውሯል የተባለው አውሮፕላን መከስከሱ ተረጋገጠ፡፡
በደረሰው የመከስከስ አደጋ ሁሉም ተሳፋሪዎች ሕይወታቸው ማለፉን የማላዊ ፕሬዚዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ ማሳወቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ንብረትነቱ የሀገሪቱ መከላከያ ሃይል የሆነ አውሮፕላን የማላዊ መዲና የሆነችውን ሊሎንግዌን እንደለቀቀ ከራዳር ውጭ መሆኑ ትናንት መገለጹ ይታወሳል።
የአቪዬሽን ባለስልጣናት ከራዳር ውጭ ከሆነችው አውሮፕላን ጋር መገናኘት አለመቻላቸውን ማሳወቃቸውን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ የአውሮፕላኗ ፍለጋና የነፍስ አድን ተግባር እንዲከናወን ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር።
በዚህም መሰረት ትናንት ምሽቱን እና ዛሬ ረፋድ ድረስ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በቺንካንጋዋ ደን ውስጥ ፍለጋ ሲያደርጉ መቆየታቸው ተገልጿል።
በዚህም አውሮፕላኗ ተከስክሳ መገኘቷን ፕሬዚዳንቱ በሰጡት መግለጫ ጠቅሰው፤ በደረሰው አሰቃቂ አደጋ እጅግ ሀዘን ተሰምቶናል ብለዋል።