አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዩክሬን ከምዕራባውያን አጋሮቿ ከምትቀበላቸው ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶች መካከል የተወሰኑትን ከሩሲያ ጥቃት ለመከላከል በውጭ ሀገራት የጦር ሰፈር ልታቆይ እንደምትችል አንድ የዩክሬን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ተናግረዋል።
ቤልጂየም፣ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድስ እና ኖርዌይ ከሩሲያ ጥቃት ለመከላከል ከ60 በላይ አሜሪካ ሰራሽ ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶችን ለዩክሬን ለመስጠት ወስነዋል፡፡
የዩክሬን አብራሪዎችም በዚህ ዓመት መጨረሻ ይደረጋል ተብሎ ከሚጠበቀው ርክክብ ቀድመው የጦር አውሮፕላኖቹን ለማብረር ስልጠና እየወሰዱ መሆኑ ተገልጿል።
በዩክሬን አየር ኃይል የአቪዬሽን ኃላፊ የሆኑት ሰርሂ ሆሉትሶቭ÷ የሩሲያ ጥቃት ዒላማ እንዳይሆኑ የተወሰኑ አውሮፕላኖች ከዩክሬን ውጭ ባሉ አስተማማኝ የአየር ማረፊያዎች ይቆያሉ ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን÷ የጦር አውሮፕላኖቹን የሚያስተናግዱ ከሆነ ሞስኮ በኔቶ ሀገራት በሚገኙ ተቋማት ላይ ጥቃት ልትሰነዝር እንደምትችል አስጠንቅቀዋል።
ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶች የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን የመሸከም አቅም ስላላቸው ለውጊያ በምናደርገው ዝግጅት ያንን ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን ማለታቸውን ኤል ቢ ሲ ዘግቧል፡፡
ምን ያህል የዩክሬን አየር ማረፊያዎች እነዚህን መስፈርቶች ሊያሟሉ እንደሚችሉ ግልጽ አይደለም ያሉት ፑቲን÷ ነገር ግን ጄቶቹ እንደደረሱ እነሱን የሚያስተናግዱትን ጥቂቶቹንም ቢሆን ሩሲያ በፍጥነት ዒላማ እንደምታደርግ ተናግረዋል፡፡