አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል ከመደመር ትውልድ መፅሀፍ ሽያጭ ገቢ እየተገነባ የሚገኘው የሐረር ኢኮ ቱሪዝም ፓርክ 86 በመቶ መድረሱን የክልሉ ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመደመር ትውልድ መፅሀፍ ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ለኢኮ ቱሪዝም ፓርክ ግንባታ እንዲውል በስጦታ ማበርከታቸው ይታወሳል።
በዚህም ሐረሪ ክልል በክልሉ ከሚገኙ የመስህብ ስፍራዎች መካከል ጅብን የማብላት ትርኢት ማሳያ ስፍራን ለቱሪስቶች ምቹ ለማድረግ የኢኮ ቱሪዝም ፓርክ ግንባታ እያከናወነ ይገኛል።
የሐረሪ ክልል ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ የኢኮ ፖርክ ግንባታው 86 በመቶ መድረሱንም አስታውቋል ።
የፓርኩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በ 2 ነጥብ 4 ሄክታር መሬት ላይ እየተካሄደ እንደሚገኝ በቢሮው የቱሪዝም ዳይሬክተርና የኢኮ ቱሪዝም ፓርክ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አሚር ረመዳን ተናግረዋል፡፡
ኢኮ ፓርኩ በውስጡ የጅብ ትርዒት ማሳያን ጨምሮ የቅርስ ስዕል ስብስቦችን የያዘ ጋላሪ፣ ሙዚየም ፣ባህላዊና ዘመናዊ ካፍቴሪያዎች እንዲሁም የተለያዩ የመዝናኛ ስፍራዎችን ያካተተ መሆኑን አብራርተዋል።
ለኢኮ ፓርኩ ግንባታ ከ140 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበትም ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል ።
ስምንት ወራት ባስቆጠረው የግንባታ ሂደትም ከ100 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩም ተገልጿል።
በእዮናዳብ አንዱአለም