Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሩሲያ የካንሰር ክትባት የሙከራ ሂደትን በማጠናቀቅ ላይ መሆኗን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ተመራማሪዎች በካንሰር ላይ የክትባት ሙከራን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስትር ሚካሂል ሙራሽኮ አስታውቀዋል።
 
ክትባቱ በጋማሌያ ኤፒዲሚዮሎጂ እና ማይክሮባዮሎጂ ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ብሉኪን የካንሰር ማእከል እና በሄርሰን ኦንኮሎጂካል ምርምር ኢንስቲትዩት በጋራ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
 
በመንግስት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት የካንሰር በሽታ መከላከያ ክትባት ምርምር በበርካታ የሳይንስ ባለሙያ ቡድኖች በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
 
ክትባቱ ቅድመ ክሊኒካዊ ሙከራዎችን እያካሄደ እንደሆነ እና የመጀመሪያዎቹ ውጤቶችም በዓመቱ መጨረሻ ይታወቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
 
ከዚያም ክሊኒካዊ ሙከራዎች እንደሚጀመሩ ሚካሂል ሙራሽኮ ከዓለም አቀፉ ኢኮኖሚክ ጉባኤ ጎን ለጎን ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
 
የጋማሌያ ኢንስቲትዩት ኃላፊ አሌክሳንደር ጂንስበርግ ክትባቱን በተመለከተ ባለፈው ሳምንት ለመገናኛ ብዙሃን ሲገልጹ÷ አስቀድሞ በካንሰር ለተያዙ ሰዎች የሚሰጥ የሕክምና ክትባት መሆኑን ተናግረዋል።
 
ክትባቱ የተፈጠረዉ በኤምአርኤንኤ ቴክኖሎጂ መሰረት እንደሆነና ቀድሞዉኑ በመድሀኒት አምራቾቹ ፋይዘር እና ሞደርና የኮቪድ-19 ክትባቶችን ለመስራት ይጠቀሙበት እንደነበር ጠቅሰዋል።
 
ጂንስበርግ አዲሱ ክትባት ለማንኛውም አይነት የካንሰር ህመም ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚችልም መናገራቸውን አር ቲ ዘግቧል።
Exit mobile version