የሀገር ውስጥ ዜና

የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚቻለው ከተረጂነት አስተሳሰብ መውጣት ሲቻል መሆኑ ተመላከተ

By Amele Demsew

June 09, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚቻለው ከተረጂነት አስተሳሰብ መውጣት ሲቻል መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ገለጹ።

“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር” በሚል መሪ ሐሳብ በሠመራ ሎጊያ ከተማ የህዝብ ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በህዝባዊ የውይይት መድረኩ ላይ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ እንደገለጹት÷ከተረጂነት አስተሳሰብ ጨርሶ ለመውጣት የልማት ስራዎችን ማቀላጠፍ ይገባል፡፡

የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚቻለው ከተረጂነት አስተሳሰብ መውጣት ሲቻል ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር ጠቅላላ የማምረት አቅማችን ከፍተኛ መሆኑ የታወቀ ነው ያሉት ሚኒስትሯ ÷የበጋ የመስኖ ስንዴን እንደ አብነት ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱ ሙሳ በበኩላቸው÷ በአካባቢያችን የሚገኙ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በመጠቀም በተጠናከረ ልማት የማስተሳሰር ስራ ይሰራል ብለዋል።