አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ፕሬዚዳንት አብዲአዚዝ ሀሰን ለፍተግሬን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰላም ማስከበር ተሰማርቶ በባይድዋ ያለውን የሶማሊያ ሕዝብ ሰላም ለማረጋገጥ እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ምስጋና አቀረቡ፡፡
ፕሬዚዳንቱ በባይድዋ ሴክተር 3 የሚገኘውን የባይድዋ አውሮፕላን ማረፊያ ከጎበኙ በኋላ÷ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ጋር በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ ላይ መክረዋል።
በውይይታቸውም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሰላም ማስከበር ውጪም ሆነ በሰላም ማስከበር ተሰማርቶ በባይድዋ የሚገኘውን የሶማሊያ ሕዝብ ሰላም ለማረጋገጥ ለከፈለው መስዋዕትነት አመስግነዋል፡፡
በተጨማሪም “ሰላምን ለማምጣት ራሳችንን እንድንችል የፀጥታ ኃይላችንን በማሰልጠን ትልቁን ድርሻ ስለተወጣ እናመሠግናለን” ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡
የሴክተር 3 ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ሰቦቃ በቀለ በበኩላቸው ÷ ሠላም አሥከባሪ ሰራዊቱ ያለ ዕረፍት ከክልሉ የፀጥታ ኃይል ጋር እየሠራ መሆኑን እና ይህንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡