አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል በሰብል ልማት የተጀመረው ንቅናቄ ከምርታማነቱ ባሻገር ከተረጂነት ወደ ልማት የሚል ማህበረሰብ አቀፍ የእሳቤ ለውጥ ማምጣቱን ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ገለጹ።
በዘንድሮው ዓመት ብቻ በክልሉ በ8 ቢሊየን ብር የተለያዩ የመስኖ ፕሮጀክቶች ትግበራ መጀመሩንም ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ክልሉ ዋቢ ሸበሌ፣ ገናሌ፣ ዳዋና ዌብ ወንዞችን ጨምሮ በርካታ የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውሃ ቢኖረውም ጸጋውን ወደ ልማት በመለወጥ ረገድ ሰፊ ክፍተት እንደነበር ጠቅሰው፥ አሁን ላይ ተስፋ ሰጭ ለውጦች አሉ ብለዋል።
ክልሉ ለእርሻ የሚውል 10 ሚሊየን ሄክታር መሬት ቢኖረውም ከለውጡ በፊት 400 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ ይለማ እንደነበር አስታውሰው፥ ከለውጡ ወዲህ የሚለማው መሬት 900 ሺህ ሄክታር መድረሱን አንስተዋል።
በዚህም ዓመታዊ የሰብል ምርትን ከነበረበት 10 ሚሊየን ኩንታል ወደ 26 ሚሊየን ኩንታል ማሳደግ መቻሉን አብራርተዋል።
በቀጣይም የእርሻ መሬት ሽፋኑን ወደ 1 ሚሊየን ሄክታር ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ከለውጡ ወዲህ የክልሉን ወንዞች ለመስኖ ልማት በማዋል ለሀገር ጥቅም እንዲውሉ የሚያስችሉ ግዙፍ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም በተያዘው ዓመት ብቻ በሀገር ምርታማነት ላይ ትልቅ ውጤት ያመጣሉ ተብለው የሚጠበቁ የመስኖ ፕሮጀክቶች በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በ8 ቢሊየን ብር ግንባታቸው እየተሳለጠ ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ የክልሉን ያልታረሰ መሬት በማረስ፣ ህብረተሰቡን ከተረጂነት ወደ ልማት በማሸጋገር ትልቅ የአስተሳሰብ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።