አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በመጠቀም ከተረጂነት ለመላቀቅ የሚደረጉ ጥረቶችን ማበረታታት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፤ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር” በሚል መሪ ሐሳብ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች÷ በሰመራ፣ ሐረር፣ ሻሸመኔ፣ ሸገር፣ ጋምቤላ ጂግጂጋ እና በሆሳዕና ከተሞች እየተካሄዱ ነው፡፡
በሰመራ እየተካሄደ በሚገኘው መድረክ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ እና የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ተገኝተዋል፡፡
አቶ ኡሞድ በመድረኩ እንደገለፁት÷ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ያሉንን ፀጋዎች በአግባቡ አውቀን ልንጠቀምባቸው ይባል ብለዋል፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ለቀጣዩ ትውልድ ከዕዳ የተላቀቀች ሀገር ለማስተላለፍ መትጋት እንደሚገባ በሐረር ከተማ እየተካሄደ ባለው መድረክ ላይ ተናግረዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ታንኳይ ጆክ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግና ከተረጂነት አስተሳሰብ መላቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
በተመሳሳይ በሻሸመኔ መድረክ ላይ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የማኅበራዊ ክላስተር ዘርፍ አስተባባሪ አብዱልሀኪም ሙሉ ተገኝተዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር÷ ውይይቱ ከተረጂነት ፈጥኖ ለመላቀቅ እና ወደ ተጨባጭ ሥራ ለመግባት እንደ ሀገር የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል፡፡
ሻሸመኔ ከተማን ጨምሮ ከምዕራብ አርሲ፣ ቦረና፣ ጉጂና ባሌ ዞኖች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በውይይቱ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
እንዲሁም በሸገር ከተማ አሥተዳደር እየተካሄደ ባለው መድረክ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰውን ጨምሮ የፌደራል፣ የክልልና የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገ/መስቀል ጫላ በጋምቤላ ከተማ በተካሄደው መድረክ እንዳሉት÷ የተረጂነትና የልመና አስተሳሰብን በመጸየፍ በምግብ እራስን ለመቻልና የሀገርን እድገት ለማፋጠን መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ጋምቤላ ክልል ያለውን ሰፊ የመሬትና የውሃ ሀብት በማልማት ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚተርፍ መሆኑንም ገልጸዋል።
እያንዳንዱ ነዋሪ ተግቶ ከሠራ ከፍጆታ አልፎ ወደትርፍ አምራችነት የሚሸጋገርበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆንም አመልክተዋል።
እንዲሁም በጂግጂጋው መድረክ ላይ÷ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) እና የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ኢብራሂም ኡስማን ተገኝተዋል፡፡
አቶ መላኩ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ያለንን ፀጋና ጉልበት በመጠቀምና ምርታማነት በማሳደግ ከተረጂነትና ልመና መውጣት አለብን ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በሶማሌ ክልል በተሰራው አመርቂ ሥራ ሰፋፊ የግብርና፣ ዘመናዊ የእንስሳት እርባታና የልማት ስራዎች መሠራታቸውን ተመልክተናል ነው ያሉት፡፡
“የተለያዩ ሀብቶችና ምቹ መሬት እያለን ለምን ተረጂ ሆንን ብለን በቁጭት፣ በመስራት ከተረጂነትና ልመና መላቀቅ አለብን ያሉት ደግሞ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ናቸው፡፡
ለዚህም በሶማሌ ክልል ያለውን እምቅ ሀብት በመጠቀም ህዝባችንን ከድህነት ማውጣት አለብን ብለዋል።
በተመሳሳይ በሆሳዕና ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ መድረክ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ÷መንግስት የተረጂነት እሳቤን ለመቅረፍና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በሁሉም አካባቢ ሊለማ የሚችል አቅም እንዳለ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ እነዚህን አቅሞች ወደ ሀብት በመቀየር ተረጂነትን በማስወገድ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።