የሀገር ውስጥ ዜና

አራት ተቋማት በአቪዬሽን ሣይንስና ኤሮስፔስ ኢንጂነሪግ ዘርፍ በጋራ ለመስራት ተፈራረሙ

By Tamrat Bishaw

June 09, 2024

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በአቪዬሽን ሣይንስ እና ኤሮስፔስ ኢንጂነሪግ ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሠነድ ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱ የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ ልኅቀት ማሳደግ በሚችሉ የአቪዬሽን ሣይንስ እና ኤሮስፔስ ኢንጂነሪግ ዘርፍ የሚጠይቀውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በጋራ ለማፍራት ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተጀመረው ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚጠናከርበትና አራቱ ተቋማት የራሳቸውን ግብዓት የሚያደርጉበት ቦታ መለየቱም በሠነዱ ተጠቅሷል፡፡

የስምምነቱን ተግባራዊነት የሚያፋጥን ከተቋሞቹ የተውጣጣ 12 አባላት ያሉት ቴክኒካል ኮሚቴ መመረጡን የመከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡

ኮሚቴውም÷ ሀገርን የሚያዘምን፣ ተቋምን የሚያሻግር እና ትውልድን የሚጠቅም መሠረት ያለው የቴክኖሎጂ ልኅቀት የሚሸጋገርበት ተቋም ለመገንባት ኃላፊነት የተጣለባቸው አካላት በትጋት እንዲሠሩ አሳስቧል።