አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፤ ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት ክብር” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ከተሞች ሕዝባዊ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው፡፡
ውይይቶቹ እየተካሄዱ የሚገኙትም÷ በድሬዳዋ፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ደብረ ብርሃን፣ ዲላ፣ ጂማ እና ቦንጋ ከተሞች ነው፡፡
በድሬዳዋው መድረክ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተደድር ጥላሁን ከበደን ጨምሮ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድረ ጁሃር እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ከንቲባ ከድር በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ያሉንን ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ሃብቶች በመጠቀም ከድህነትና ከተረጂነት ለመላቀቅ እየተከናወኑ በሚገኙ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
እነዚህን ውጤቶች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበው÷ በተለይም በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተጀመሩትን ጥረቶች በማሳደግ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ይገባል ብለዋል፡፡
ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ያልተላቀቀችው የተረጂነት እና ልመና አስተሳሰብ ሙሉ ክብርና ሉዓላዊነቷን ነፍጓታል ብለዋል፡፡
ከተረጂነት አስተሳሰብ እንድንወጣ የልማት መርሐ-ግብሮችን ተግባራዊ ማድረግ፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ሀገር በቀል መፍትሔዎችን መዘርጋት እና የመረዳዳትእሴቶቻችን ማጎልበት፣ በተለያዩ ምክንያቶች ለተቸገሩ ወገኖች በቂ ድጋፍ ማድረግ፣ በዘላቂነትም ማቋቋም ሲቻል ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በተመሳሳይ በደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ ባለው መድረክ በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር)፣ በብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ተገኝተዋል።
አሕመዲን (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ መንግሥት ሀገርን ከድህነት የሚያወጡ ፕሮጀክቶችን መጀመሩን አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል በጅማ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ውይይት የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ÷ አባቶች ዳር ድንበሯን ጠብቀው ያስረከቡንን ኢትዮጵያ ከተረጂነት በማላቀቅ ሉዓላዊነቷን ማስከበር ይገባል ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በዲላ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው መድረክ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አወሉ አብዲ፣ በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ክላስተር አስተባባሪ አክሊሉ አዳኝ (ኢ/ር) ተገኝተዋል።
በአዳማ ከተማ መድረክ የተገኙት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ተስፋዬ በልጂጌ÷ ኢትዮጵዊያን ለአፍሪካ ነፃነት ፈር ቀዳጅ ሀገር ሆነን ሳለ ድህነትን ለመቅረፍ ባደረግነው ጥረት ግን ባለን የጀግንነት ልክ አይደለም ብለዋል።
ለዚህም ብልፅግና ፓርቲ ተረጂነት በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ያለውን ጫና ተገንዝቦ ብልፅግናን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ተረጂነትን ለማስቀረት ጠንክሮ መስራት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በእዮናዳብ አንዱአለም፣ በማርታ ጌታቸው፣ ምናለ ገበየሁ፣ አላዩ ገረመው፣ ምስክር ስናፍቅ እና በረከት ተካልኝ