አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ አስተዳደርና የቻይናዋ ጓንዡ ከተማ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን የሁለት ከተሞች የወዳጅነት መግባቢያ ሥምምነት ተፈራርመዋል።
ሥምምነቱን የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) እና የጓንዡ ከተማ የማዘጋጃዊ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ መሪ ዣዎ ዱክሲያን ተፈራርመዋል።
ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፥ የሸገር ከተማ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል መጪውን ትውልድ ታሳቢ በማድረግ እየተመሰረተ ያለ ግዙፍ ከተማ ነው።
የሸገር ከተማ ስማርት ሲቲ ሆኖ እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰው ፥ በውስጡ ልዩ የኢንዱስትሪ፣ የኢንቨስትመንት፣ የአይ ሲ ቲ፣ የሪል ስቴት፣ የቱሪዝምና ሌሎች ወሳኝ የኢኮኖሚ ኮሪደሮች አካቷል ብለዋል።
ከቻይና ጓንዡ ከተማ ጋር ዛሬ የተደረገው ይህ የመግባቢያ ሥምምነት በዚህ ረገድ ተሞክሮን ለመጋራትና በቀጣይ አብሮ መሥራት የሚያስችል መሆኑን ነው ከንቲባው ያስረዱት።
የጓንዡ ከተማ በተለይም በአረንጓዴ ልማት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በከተማ ልማት በንግድና ኢንቨስትመንት ሰፊ ተሞክሮ ያላቸውና ግዙፍ ኢኮኖሚ የገነባች ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያሟላች ከተማ መሆኗን ገልጸዋል።
በመሆኑም የሸገር ከተማ አስተዳደር ዓለም አቀፍ የከተማ መስፈርት አሟልቶ እንዲገነባ ለማድረግ ከጓንዡ ከተማ ጋር በመቀራረብ ይሰራል ነው ያሉት።
የሸገር ከተማ አስተዳደር ወደ ሠባት የሚደርሱ የኢኮኖሚ ኮሪደሮችን በመለየት እየሰራ ሲሆን ፥ ይህ ሥምምነትም ከተማውን በሚጠበቀው ልክ ለማልማት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል።
የጓንዡ ከተማ የማዘጋጃዊ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ መሪ ዣዎ ዱክሲያን በበኩላቸው እንዳሉት ፥ ጓንዡ ለቻይና ትልቅ የኢኮኖሚ አስተዋጽዖ ከሚያበረክቱት ትልልቅ ከተሞች መካከል አንዷ ናት።
ጓንዡ በተለይም በንግድ በኢንቨስትመንት በስፋት የምትታወቅ ከተማ መሆኗን አንስተው ፥ ከተማዋ ያላትን ተሞክሮና ልምድ ተጠቅማ ከሸገር ከተማ ጋር በጋራ እንደምትሰራ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።