አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በሶስተኛው የብሪክስ ሼርፓስ ስብሰባ ተካፈለ።
በዛሬው ዕለት በሩሲያ ኒዥኒ ኖቭጎሮድ በተጀመረው የብሪክስ ስብሰባ ላይ አቶ ማሞ ምህረቱ ባደረጉት ንግግር፤ ተለዋዋጭና ለመተንበይ አስቸጋሪ በሆነው የዓለም ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ከባቢ ብሪክስ ሀገራትን በማስተባበርና ሀብትን በማሰባሰብ መረጋጋት ሊፈጥር የሚችል ሃይል ሆኖ ሊወጣ እንደሚችል ገልጸዋል።
በዚህም ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን በአጋርነት መንፈስ ሊፈታ እንደሚችል ጠቁመዋል።
አካታችና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በብሪክስ አባላት ሀገሮች ዘንድ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝም ፍሰት፣ ግንኙነትን እንዲሁም የፋይናንስ አቅምን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አዲሱ የልማት ባንክ ስራ ሲጀምር ኢትዮጵያ ለመቀላቀል ዝግጁ መሆኗን አንስተው፤ የባንኩ ቅድመ ሁኔታዎች ኢትዮጵያ ከያዘው የእድገት ጎዳና ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።