አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ5 እናቶች አንዷ በእርግዝና ጊዜ ለሚከሰት የስኳር ህመም ተጋላጭ ናት።
የእናት ጤንነት እና የጽንስ ደህንነትን ለማረጋገጥ ስኳርን በጥብቅና በጊዜ መቆጣጠር አስፈላጊ ነው።
የስኳር ህመም ላለባት ነፍሰጡር እናት የስኳር መጠንን ለመቆጣጠር የተወሰኑ አማራጮች ቢኖሩም በጣም ተመራጭ የሆነው ሕክምና ኢንሱሊን ነው።
ከሌሎች የሚዋጡ መድሐኒቶች ይልቅ ኢንሱሊን የሚመረጥባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
1. ኢንሱሊን ለእናትም ለጽንስም ደህንነት ፡- ኢንሱሊን በእርግዝና ወቅት የስኳር በሽታን ለመቆጣጠር አስተማማኝ መድሃኒት ነው። የእንግዴ ልጁን ማለፍ ስለማይችል በማደግ ላይ ያለውን ጽንስ አይጎዳውም።
2. ኢንሱሊን የስኳር መጠንን በተሻለ ለመቆጣጠር ያስችላል ፤ በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን መዋዠቅ በጽንሱ ላይ አደጋን ሊፈጥር ቢችልም ኢንሱሊን ስኳሩን በታለመለት ግብ ውስጥ የተረጋጋ መሆኑን ያረጋግጣል።
3. በተጨማሪም እንደ እርግዝናው ጊዜያት የእናትየዋን ተለዋዋጭ ፍላጎቶች ለማሟላት ኢንሱሊን ከአፍ ከሚወሰዱ መድሐኒቶች በበለጠ ይመቻል።
አብዛኛዎቹ ነፍሰ ጡር እናቶች ኢንሱሊንን ሆድ ላይ ለመወጋት ይፈራሉ፣ መርፌው ጽንሱን ይጎዳዋል ብለውም ይጨነቃሉ።
የስኳር ህመም ላለባቸው ነፍሰ ጡር እናቶች ኢንሱሊን ለመውጋት ተመራጩ ቦታ ሆድ እንደሆነ ይነገራል።
የኢንሱሊን መርፌው ለጽንሱ ምንም አይነት ስጋት አይፈጥርም፣ ምክንያቱም ማህፀኑ ጽንሱን በበቂ ሁኔታ ከለላ ይሰጠዋል ይላል መረጃው።
በእርግዝና ወቅት ኢንሱሊንን ሆድ ላይ የመወጋት ደህንነት ከተረጋገጠ ቀጥሎ በተለያዩ የእርግዝና ወቅቶች መደረግ ስላለባቸው የተወሰኑ ምክሮች እንመልከት፡-
– በመጀመሪያው የሦስት ወራት የእርግዝና ጊዜ የኢንሱሊን መርፌ በየትኛውም የሰውነት ክፍል ላይ መወጋት ይቻላል፡፡
– ከእርግዝና በፊት የነበረ ስኳር ያለባቸውና ኢንሱሊን የሚወስዱ እናቶች በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የኢንሱሊን መውጊያ ቦታ ወይም ቴክኒክ ለውጥ አያስፈልግም።
– በሁለተኛው ሦስት ወራት ጊዜ ሲደርስ የሆድ ገጽታ መለወጥ ይጀምራል፤ ጽንሱ ያድጋል፣ ሆድም እንዲሁ። በዚህም የመርፌ መወጊያ ቦታን መጠነኛ ማስተካከያ ማድረግ ይኖርብዎታል። በእምብርት ዙሪያ ከጽንሱ ፊት ለፊት ያለውን የሆድ ክፍል ሳይሆን ጽንሱ ካለበት በደንብ ራቅ ብለው ከጎን ያሉት የሆድ ክፍሎች ላይ ኢንሱሊንን መወጋት ይችላሉ።
– በመጨረሻ ሦስተኛው ወር ልጁ እያደገ የመርፌ መወጊያ ቦታ እየጠበበ ይሄዳል፤ እንዲሁም ቆዳ በሆድ ላይ በጣም ጥብቅ ሊል ይችላል። እንዳንዴ ለኢንሱሊን መርፌ መወጊያ የሚሆን ምቹ ቦታ ማግኘት ሊከብድ ይችላል። መምረጥ ያለብዎት ቦታ በጎን የሆድ ክፍል ያለውን መሆን አለበት። ቦታውን በአውራ ጣት እና ጠቋሚ ጣት መሀል ቆንጠጥ በማድረግ ቆዳውን ትንሽ በማንሳት መወጋት ይቻላል፡፡መርፌውን ከቆዳ በ90 ዲግሪ ቀጥታ አስገብቶ መውጋት ይቻላል። ይህ ዘዴ ምቹ እና ውጤታማ ሲሆን ፥ የኢንሱሊን መርፌን ለመወጋት ተመራጭ መንገድ ነው።
– ከተገኘ በጣም አጭር የኢንሱሊን መርፌ መጠቀም ይመከራል። ይህን የማይመርጡ እና ጽንሱን እንዳልወጋው የሚል ከፍተኛ ፍርሃት ያለባቸው እናቶች እንደ አማራጭ ክንድ፣ ታፋ ወይም መቀመጫ ላይ ሊወጉ ይችላሉ።
– ከጤና ባለሙያ ጋር በመካከር እንደ አስፈላጊነቱ የኢንሱሊን መጠንን ለማስተካከል የደም ውስጥ የግሉኮስ መጠንን በየጊዜው መከታተል አስፈላጊ እንደሆነ ይነገራል፡፡
– በተጨማሪም መደበኛ የቅድመ ወሊድ ህክምናዎትን መከታተልዎን መቀጠል ይገባል ሲል የመከረው የአዲስ አበባ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ነው።