አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዲሞክራሲ ተቋማት ህግና ስርዓትን በመከተል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር እንዲቆሙ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ጥሪ አቀረቡ፡፡
“የዴሞክራሲ ተቋማት በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ ያላቸው ሚና” በሚል ሃሳብ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የዴሞክራሲ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ለሁለት ቀናት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል።
በስልጠናው ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እና ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶን ጨምሮ የክልሎች እና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች እና የዴሞክራሲ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ÷ የዴሞክራሲ ተቋማት ለሀገርና ህዝብ ጥቅም መከበር ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸው ፥ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ስኬታማነት አስፈላጊ ሚና አላቸውም ብለዋል።
ለዚህም መንግስት የዴሞክራሲ ተቋማት ነፃና ገለልተኛነታቸው ተጠብቆ የሚሰሩበትን የአሰራር፣ የሰው ሃይል እና የአደረጃጀት ማሻሻያ በማድረግ ምቹ ምኅዳር መፍጠሩን ገልጸዋል።
ተቋማቱም ህግና ስርዓትን በመከተል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር በመትጋት ለሀገር ልማትና ሰላም አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደትም ትብብርና መናበብን በማስፋት ሚዛናዊነት የተላበሰና የህዝብን ጥቅም ያስቀደመ ስራ መስራት ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።