የሀገር ውስጥ ዜና

አባት፣ እናትና አጎቱን በመግደልና ወንድሙን በማቁሰል ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በሞት እንዲቀጣ ተወሰነ

By Tamrat Bishaw

June 05, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አባት፣ እናትና አጎቱን በመግደል እንዲሁም ወንድሙን በማቁሰል ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ በሞት እንዲቀጣ መወሰኑን የኮንሶ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

ወንጀሉ የተፈጸመው በኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ ሰገን ገነት ቀበሌ ሰገንዶዴ መንደር መሆኑ ተገልጿል።

ተከሳሹ ካፍታ ካፈላ ታህሳስ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡30 ሰዓት አካባቢ ቤተሰቦቼ ገንዘብ ከለከሉኝ በሚል ምክንያት ከጓደኛው ጦር መሳሪያ በመውሰድ አባት፣ እናቱንና አጎቱን ተኩሶ የገደለና ወንድሙን ያቆሰለ መሆኑን ባጣራው ምርመራ ማረጋገጡን የኮንሶ ዞን ፖሊስ ገልጿል።

ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ አካሂዶ መዝገቡን ለዞን ዐቃቤ ሕግ አቅርቦ ዐቃቤ ህግም በሰው መግደል ወንጀል ክስ መስርቶ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቧል።

ከዐቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገብ የደረሰው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የክስ ሂደቱን ሲመለከት ቆይቶ ተከሳሹ ግለሰብ ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጧል።

በዚሁ መሠረት የኮንሶ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሽ ካፍታ ካፋላ በተከሰሰበት ወንጀል ድርጊት ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በሞት እንዲቀጣ መወሰኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል።

በተከሳሹ ላይ የተጣለው የሞት ፍርድ በሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሲጸድቅ ተፈጻሚ ይሆናል።