አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤንች ብሔረሰብ አባላት ከተፈጥሮ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው። የተፈጥሮ ዑደትን ከቱባው ባህላዊ እሴታቸው ጋር አመሳጥረው ዓመትን በመቀየር ወደ አዲስ የዘመን ምዕራፍ ይሻገራሉ።
ወደ አዲስ ዘመን ሲሸጋገሩ ለፈጣሪ ታላቅ ምስጋናን ያቀርባሉ። ይህ የምስጋና በዓል ‘ቢስት ባር’ የሚባል ሲሆን፤ “ቢስት” ማለት የበኩር ወይም የመጀመሪያ፣ “ባር” የሚለው ቃል ደግሞ በዓል የሚል ትርጉም አለው።
በአጠቃላይ በዓሉ የበኩር/የመጀመሪያ በዓል ማለት ሲሆን፤ የሚከበረው በጥቅምት ያሸተው አዝመራ ከህዳር አጋማሽ እስከ ታህሳስ ባለው ጊዜ ውስጥ ደርሶ ፍሬ መጠስት ሲጀምር ነው ይላሉ የቤንች ሸኮ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ጌታቸው ኮይካ።
በዚህ ወቅት ፍሬ መስጠት የጀመረው የበኩር አዝመራ ይቀመሳል። የቤንች ብሄር አባላት የመጀመሪያ ወይም የበኩር የሆነውን እህል ሲቀምሱ ብኩርና ቅድሚያ ይሰጠዋል።
የደረሰውን እህል ቅድሚያ የሚቀምሰው በቤተሰቡ ውስጥ በኩር የሆነው ሰው ነው። አያት ካለ አያት ከሌለ አባት አባት ከሌለ ታላቅ የሆነ የቤተሰቡ አባል ቅድሚያ ይሰጠዋል። ከዛ እህል የመቅመስ ስርዓቱ በቤተሰብ ውስጥ በዕድሜ ተዋረድ ይቀጥላል።
እህል ከተቀመሰ በኋላ በቀዬው ያሉ ሰዎች በጋራ ተሰብስበው የቅምሻ ስርዓትን ይከውናሉ። እህል ሁሉም ዘንድ እኩል አይደርስምና ቀድሞ የደረሰለት ቤተሰብ ለሌላው ጎረቤቱ ከደረሰው እህል የማካፈል ግዴታ አለበት። ለብቻ እህል መቅመስ እንደ ነውር ይቆጠራል። ይህ የቤንች ብሄረሰብ ለአብሮነትና ለመተሳሰብ የሚሰጠውን ቦታ የሚያሳይ የቢስት ባር ሌላው እሴት ነው።
ቢስት ባር ወደ አዲስ የዘመን ምዕራፍ መሻገር የሚበሰርበት ብኩርና ክብሩ ከፍ የሚልበት፣ አብሮነት የሚነግስበት ድንቅ ባህላዊ እሴት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ለፈጣሪ ታላቅ ምስጋና የሚቀርብበት በዓል ነው።
የቤንች ብሄር አባላት በሶስት ምክንያቶች ለፈጣሪ ምስጋና እንደሚያቀርቡ የሚገልጹት አቶ ጌታቸው ኮይካ፤ የመጀመሪያው ምክንያት ፈጣሪ እህሉን ከበረዶ ከጎርፍና ከሌላው አደጋ ጠብቆ ፍሬ እንዲሰጥ በማድረጉ ነው ብለዋል።
ሁለተኛው ምክንያት ህዝቡ ሰላምና ጤና ሆኖ ወደ አዲስ የዘመን ምዕራፍ በመሻገሩ የሚቀርብ ምስጋና ሲሆን፤ ሶስተኛው ደግሞ ከክረምት ጎርፍ ነጎድጓድና ጭቃ አልፎ የጸደይ ጸሀይ ያደመቀችው አዲስ ቀን በመምጣቱ ለፈጣሪ የሚቀርብ ምስጋና ነው።
ቢስት ባር ደስታና ፈንጠዝያ በቤንች ቀዬ የሚናኝበት አዲስ ተስፋ ከአዲስ ብርሃናማና ብሩህ ቀን ጋር አብሮ የሚወለድበት በዓል ነው። ይህ በዓል ለዘመናት በቀደሙ አባቶች ሲከበር ኖሮ በተለያዩ ምክንያቶች በዓሉ ሳይከበር ለአያሌ አመታት ተቋርጦ ቆይቷል።
ቢስት ባር ከተቋረጠ ከረጅም ዓመት በኋላ በተደራጀ መንገድ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከግንቦት 29 እስከ ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም በድምቀት ሊከበር ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጓል።
የቤንች ብሄረሰብ አባላትና የአካባቢው ተወላጆችና ሌሎች እንግዶችም ቢስት ባርን ፍቅር ባስተሳሰረው አብሮነት ለማክበር ጉጉታቸው አይሏል።
በተስፋዬ ምሬሳ