የሀገር ውስጥ ዜና

ለምስራቅ ዕዝ አመራሮች የሽምቅና የፀረ-ሽምቅ የግንዛቤ ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጠ

By Amele Demsew

June 04, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለምስራቅ ዕዝ አመራሮች በብርሸለቆ የሽምቅና የፀረ-ሽምቅ የግንዛቤ ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ስልጠናውን በበየነ መረብ የሰጡት የባህርዳር-ጎንደር ኮማንድፖስት ሰብሳቢና የሰሜን ምዕራብ እዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ብርሃኑ በቀለ ÷ የአማራ ክልልን ወደ ቀደመ ሰላሙ ለመመለስና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ፅንፈኛውን ከህዝቡ ነጥሎ መደምሰስ የሰራዊቱ ቀዳሚ ግዳጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጄነራል መኮንኑ አመራሮች ከስልጠናው ያገኙትን አቅም ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ በቀጣናው የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሰላም ሀይሎችንና ፅንፈኞችን በአጭር ጊዜ ለማጥፋት የአመራር ሚናቸውን በብቃት መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ሠራዊቱ የወሰደውን ስልጠና በመጠቀም ነፍጥ ያነገበውን የአማራ ክልል ፅንፈኛ በማሳደድ ፣ በመክበብና በመደምሰስ ሰላም በማምጣት ክልሉን ወደነበረበት መረጋጋት ማምጣት እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘው መረጃ ያመላክታል ፡፡

ጽንፈኛው የፖለቲካ ዓላማ የሌለው ነው ያሉት ሌተናል ጄነራል ብርሀኑ ÷ ሸማቂው ህብረተሰቡን እየገደለ ፣እያገተ፣ መሰረተ ልማት እያወደመ፣ እየዘረፈና ህዝቡ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ መንገድ እየዘጋ መኖር እንደማይችል አረጋግጠዋል፡፡