አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኳታሩ ዶክ ህክምና ማዕከል በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ መዋዕለንዋዩን ለማፍሰስ ያለውን ፍላጎት ገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኳታር ዶሃ ከሚገኘው የዶክ ህክምና ማዕከል መስራች ዶ/ር ኢማኑኤል ቶሎሳ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ÷ የህክምና ማዕከሉ በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ መሰማራት በሚችልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል ።
የህክምና ማዕከሉ በአይነቱ ልዩ የሆነ እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የአጥንት ህክምና ማዕከል በኢትዮጵያ ለማቋቋም ፍላጎት እንዳለው መገለጹን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
የህክምና ማዕከሉ በኳታር ከኦርቶፔዲክ፣ ከሩማቶሎጂ፣ ከኒውሮሎጂ፣ ኒውሮፊዚዮሎጂ፣ ፊዚዮቴራፒ፣ ካይሮፕራክቲክ እና የጥርስ ህክምና ጋር የተያያዙ የምርመራና የህክምና አገልግሎቶችን የሚሰጥ ትልቁ የጤና ማዕከል መሆኑ ተገልጿል፡፡