አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና የልዑካን ቡድናቸው በሶማሊያ እና በሶማሌላንድ ግንኙነት ዙሪያ በሚደረገው የምክክር መድረክ ላይ የነበረውን ተሳትፎ አጠናቆ ዛሬ ተመለሰ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ነበር ለውይይቱ ጅቡቲ የገቡት
በሶማሊያ እና በሶማሌላንድ ግንኙነት ዙሪያ በጅቡቲ የተካሄደው የምክክር ጉባኤው በየካቲት 2012 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ የተደረገው ውይይት ተከታይ ክፍል ነው።
በምክክር መድረኩ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የጅቡቱ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ እና የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሳ ቢሂ አብዲ እና የኢዳግ ዋና ፀሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተገኝተዋል።
በዚሁ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ዕርቅን ማውረድ ለቀጠናው ውህደት መሠረት እንደሆነ መግለፃቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መረጃ አመላክቷል።
“ትብብር እና ሰላም በግንባር ቀደምነት ከተተገበሩ ውጤታማ በሆነ መንገድ የቀጠናውን ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል የተትረፈረፈ ሀብት አለ” ብለዋል።
“የድህነት እና የተስፋ መቁረጥን ዑደት ለመሻር ሃብታችንን ማሰባሰብ እንችላለን” ሲሉም ተናግረዋል።