አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደብረብርሃን ከተማ የተገነባው ፊቤላ ኢንዱስትሪያል የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ተመረቀ፡፡
በምርቃት ስነስረዓቱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የተገነባው ይህ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪናዎችን የሚገጣጥም ሲሆን 3 ቢሊየን ብር ወጭ ተደርጎበታል።
ፋብሪካው በዓመት 1 ሺህ ተሽከርካሪዎችን የሚገጣጥም መሆኑን የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰጠኝ እንግዳው ገልጸዋል።
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር ለ1 ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በወቅቱ እንዳሉት÷ የመኪና መገጣጠሚያው የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት እና የስራ እድል ለመፍጠር የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል።
ፋብሪካው በሁለት አመታት ውስጥ ተገንብቶ መጠናቀቁ ለሌሎች አረአያ እንደሚሆን ገልጸው፤ የክልሉን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በእቅድ በመምራት መሬት የወሰዱ ፋብሪካዎች ፈጥነው ወደ ማምረት እንዲገቡ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።