አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)ማሻሻያ ተደርጎበት የፀደቀዉ ዓለም አቀፉ የጤና ህግ ለድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ወረርሽኝ ቁጥጥር፣ ዝግጁነትና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያግዛል ሲሉ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለፁ፡፡
በጄኔቫ ስዊዘርላንድ ሲካሄድ የነበረው 77 ኛው የዓለም ጤና ጉባኤ በ2005 ዓለም አቀፍ የጤና ህግ ላይ የተደረገዉን ማሻሻያ በማጽደቅ ተጠናቋል።
ዓለምአቀፉ የጤና ህግ በዋናነት በህብረተሰብ ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ወቅት የሀገራት ዝግጁነትና ምላሽ አሰጣጥ አቅምን ለማሻሻል እንዲሁም አለም አቀፍ ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ታሳቢ ያደረገ ነዉ ተብሏል።
ይህም ድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋና ወረርኝ ሲከሰት ፍትኃዊ የሆነ አቅርቦት እንዲኖርና ሀብት በማሰባሰብ ታዳጊ ሀገራትን ለመደገፍ ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
የቀረበዉ ማሻሻያ በጉባኤዉ ተቀባይነት አግኝቶ መጽደቁ ግብአት ፍትኃዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ እንዲደረግ እና ቀጣይ የጤና ወረርሽኝ ስጋቶችን አለም በጋራ በመቆም መከላከል እንዲችል የሚያደርግ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በጉባኤዉ የአፍሪካ አባል ሀገራትን በመወከል ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ÷ ዓለም አቀፍ የጤና ህግ አገራት ከተባበሩና በጋራ ከሰሩ ለጋራ ዓላማ በጋራ መቆም እንደሚቻል አይነተኛ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ህጉ ለድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ወረርሽኝ ቅኝትና ቁጥጥር፣ ዝግጁነት እንዲሁም ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እጅጉን እንደሚያግዝ መናገራቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡