አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 10 ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ 210 ሺህ ቶን ቡና 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው የቡና ምርት በየዓመቱ እየጨመረ ነው።
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት 10 ወራትም 210 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ መቅረቡን ገልጸው በዚህም 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ነው ያስረዱት።
ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ ከ50 እስከ 60 ለሚሆኑ የውጭ ሀገራት ቡና የምትልክ መሆኑን ገልጸው አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ቢልጂየም፣ ጀርመንና ሳኡዲ አረብያ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡና በብዛት ወደ ሀገራቸው የሚያስገቡና የሚጠቀሙ ሀገራት ናቸው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ሀገራት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ከቡና ንግድ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለማስቀረትና የዘርፉን የውጭ ንግድ አፈጻጸም ለማሳደግም ዘመናዊ አሰራር መተግበሩን ጠቁመዋል።