ዓለምአቀፋዊ ዜና

በሜክሲኮ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ተመረጡ

By Meseret Awoke

June 03, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ክላውዲያ ሺንባም በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ ድምጽ በማሸነፍ የሜክሲኮ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል።

ክላውዲያ ሺንባም በፈረንጆቹ ጥቅምት 1 ቀን 2024 ላይ ፕሬዚዳንት አንድሬስ ማኑኤል ሎፔዝ ኦብራዶርን ይተካሉ ተብሏል።

የቀድሞ የኢነርጂ ሳይንቲስት ሺንባም በሎፔዝ ኦብራዶር የተሰሩትን ስራዎች እንደሚያስቀጥሉ ቃል ገብተዋል እንደ ቢቢሲ ዘገባ።

ይህን ተከትሎ ባደረጉት ንግግርም መራጮችን “አላሰፈርኳችሁም” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የተመራጯ ፕሬዚዳንት ደጋፊዎች “ፕሬዚዳንት ክላውዲያ ሺንባም” የሚል ባነሮችን እያውለበለቡ በሜክሲኮ ከተማ ዋና አደባባይ ድሉን በማክበር ላይ እንደሆኑም ተጠቁሟል።

ሺንባም ለፕሬዚዳንትነት ከመወዳደራቸው በፊት የሜክሲኮ ከተማ ከንቲባ የነበሩ ሲሆን፥ በሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካላቸው ኃላፊነቶች አንዱና ለፕሬዚዳንትነት መንገድ ጠራጊ ነው ይባላል፡፡