አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “አሜሪካ በኢንዶ-ፓስፊክ ስትራቴጂ በኩል በቀጣናው የበላይነቷን ለማስጠበቅ ‘የእስያ-ኔቶ’ ለመገንባት ትፈልጋለች” ሲል የቻይና መከላከያ ባለሥልጣን ወነጀለ፡፡
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ አውስቲን በ21ኛው የሻንግሪላ ውይይት “ኢንዶ-ፓሲፊክ ስትራቴጂ” ላይ በመገናኛ ብዙኃን ላደረጉት ንግግር÷ የቻይና ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮሚሽን የጋራ ሠራተኞች መምሪያ ምክትል ኃላፊ ሌተናንት ጄኔራል ጂንግ ጂያንፌንግ ምላሽ ሰጥተዋል።
በምላሻቸውም “የአሜሪካ ‘ኢንዶ-ፓሲፊክ ስትራቴጂ’ የቀዝቃዛው ጦርነት አስተሳሰብን እና የዜሮ ድምር ጨዋታን የያዘ በቀጣናዊ ትብብር ስም ብቸኛ ተጠቃሚ ለመሆን የሚደረግን ጥረት አመላካች” ነው ብለዋል።
የዚህ እውነተኛ ዓላማም በአሜሪካ የሚመራና የበላይነቷን የሚያስጠብቅ ትንሹን ክብ ወደ ትልቅ ክብ በመቀላቀል የእስያ-ፓሲፊክ ሰራሽ ኔቶን መፍጠር ነው ብለዋል፡፡
ስትራቴጂው የቀጣናውን ሀገራት ሰላም፣ ልማት፣ ትብብር እና አሸናፊነትን የመሰሉ የጋራ ፍላጎቶችን የሚጻረር መሆኑን ጠቁመው÷ ይህም የአሜሪካን ራስ ወዳድ ዓለም አቀፋዊ ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ የሚያገለግል እንደሆነና ወደፊትም ፋይዳ የሌለው ስለመሆኑ መናገራቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
የቻይና ጦር ከቀጣናው ሀገራት ወታደሮች ጋር በመተባበር ስትራቴጂካዊ ግንኙነትን ለማጎልበት፣ ተግባራዊ ትብብርን ለማጠናከር፣ አዲስ እና የላቀ ጥንካሬን በማበርከት የእስያ-ፓሲፊክ ማህበረሰብን ለመገንባት በጋራ ለመስራት እንደሚፈልግ አስታውቀዋል፡፡