የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል ጽዱና ምቹ ከተማ ለመፍጠር እየተሰራ ነው ተባለ

By Amele Demsew

May 31, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ጽዱና ለመኖሪያ ምቹ ከተማን የመፍጠር ስራ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

በአረንጓዴ ልማት የተዋቡ ጽዱና ለኑሮ የተመቹ ከተሞችን ለመፍጠር ከ300 ሚሊየን ብር በላይ መመደቡም ተገልጿል።

በክልሉ የከተሞች ጽዱና አረንጓዴ ልማት መርሐ ግብር በመንግስት፣ በህዝብና በባለሃብቶች የተቀናጀ ንቅናቄ መጀመሩን አስተዳደሩ ገልጿል።

በጊዜያዊ አስተዳደሩ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የአረንጓዴ ልማትና ውበት ዳይሬክተር አዳነ ገብረፃድቅ እንዳሉት÷ በ13 ከተሞች ውብ ጽዱና ለኑሮ ምቹ የሆኑ ከተሞች ለመፍጠር የተቀናጀ ንቅናቄ ተጀምሯል።

ከተያዘው ግንቦት 2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከሚቀጥሉት የክረምት ወራት በመንገድ አካፋዮችና ዳርቻዎች ላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከተመደበው በጀት ውስጥ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነው ከባለሃብቶች የተገኘ መሆኑንና ቀሪው ገንዘብ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተመደበ መሆኑን አቶ አዳነ አስረድተዋል።

በከተሞች የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻን የማፅዳትና የማስወገድ ስራም በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል። #ጽዱኢትዮጵያ