አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በየመን በስፋት የሚንቀሳቀሱት የሁቲ አማፂያን በቀይ ባህር ዘመቻ ከጥቅምት ወር ጀምሮ 129 መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ገለፁ፡፡
የአማጺያኑ መሪ አብዱል ማሊክ አል ሀውቲ÷ ቡድኑ በአካባቢው የሚፈጽመውን ጥቃት እያሰፋ መሆኑን ገልጾ፤ ከዚህ ድርጊቱ ሊያስቆመው የሚችል ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንደማይኖር ተናግሯል።
አማጺያኑ ባለፉት ሰባት ቀናት ውስጥ 12 የተሳኩ ዘመቻዎችን በማድረግ በቀይ ባህር፣ በህንድ ውቅያኖስና በሜዲትራኒያን በሚገኙ 10 መርከቦች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውንም ገልጿል።
የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ጥምር ወታደራዊ ሀይል በወሰደው እርምጃ የሁቲ አማጺያን እንቅስቃሴ ቀንሷል በሚል በዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች የሚሰራጨው ዜና ሀሰት ነው ሲል የቡድኑ መሪ ተናግሯል።
እኛ እርምጃችን አልቀነሰም፣ ነገር ግን በአሜሪካ እና በብሪታንያ በኩል የአሰሳ እና የመርከብ እንቅስቃሴ ቀንሷል፣ የእስራኤል የባህር እንቅስቀሴ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ለመቆም ተቃርቧል ብሏል፡፡
በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ጦር የአማፂያኑን ጥቃት ለመከላከል በቀይ ባህር ዙሪያ ዘመቻ ማድረግ ከጀመረ በርካታ ወራትን ቢያስቆጥርም የአማጺያኑ ጥቃት አሁንም ስለመኖሩ አረብ ኒውስ ዘግቧል፡፡