የሀገር ውስጥ ዜና

ተመድ ለኢሜግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የማደርገውን ድጋፍ እቀጥላለሁ አለ

By Amele Demsew

May 31, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኢሜግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በሚያከናውነው የሲቪል ምዝገባ ተግባር ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በተመድ የሕጻናት ልማት ፈንድ የሕጻናት ጥበቃ ዳይሬክተር ሺማ ሰን ጉብታን ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የሲቪል ምዝገባ ሂደት፣ ተቋሙ በቀጣይ ሊሰራቸው ባሰባቸው የሲቪል ምዝገባ አዋጅ ማሻሻያ እና ምዝገባውን በማዘመን ዙሪያ መምከራቸውን የአገልግሎቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

ሺማ ሰን ጉብታን በበኩላቸው ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ በርካታ ተግባራት እንደሚያከናውን ጠቅሰው÷ ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በሚያከናውናቸው የሲቪል ምዝገባ ሥራዎችም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡