የሀገር ውስጥ ዜና

በጋራ ጉዳዮች ላይ በመምከር ለተሻለ ለውጥ መስራት ይገባል- አቶ እንዳሻው ጣሰው

By Amele Demsew

May 31, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገራዊ እና ክልላዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ በመምከር ለተሻለ ለውጥ መስራት ይገባል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ፡፡

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሆሳዕና ከተማ ውይይት አካሂደዋል፡፡

አቶ እንዳሻው ጣሰው በመድረኩ ላይ እንደገለጹት÷ በሀገራዊ እና ክልላዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ በመምከር ለተሻለ ለውጥ መስራት ይገባል።

ክልሉ በአዲስ መልክ ከተመሰረተ ወዲህ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ በሚያስችሉ ስራዎች ላይ ትኩረት መደረጉንም አስረድተዋል፡፡

ክልሉ በተረጋጋ መንገድ ስራ እንዳይጀምር የሚፈልጉ አካላትን ሴራ በማክሸፍ በተሟላ መንገድ ስራ ለመጀመር ጥረት መደረጉንም አብራርተዋል፡፡

የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ ማስጠበቅ፣ የግብርና ስራዎችን ቀጣይነት ማረጋገጥ፣ የገቢ አሰባሰብ ስርዓትን ማዘመን፣ በትምህርት፣ ጤና እና ሌሎችም ሴክተሮች ልዩ ትኩረት በማድረግ እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡

የፍትሕ ስርዓት ማሻሻያ ፕሮግራሞችን ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት ተሰርቷል ማለታቸውን የርዕሰ መሥተዳድር ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በክልሉ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን መጎብኘተቻው የትብብር መንፈስን እንደሚፈጥር አንስተዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምንም በላይ የህዝብን ጥቅም ማስቀደም ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳላባቸው አስገንዝበዋል፡፡