Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አመጋገብና ጤናን የሚያሻሽሉ ከ200 በላይ የምርምር ስራዎች መሰራታቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ዓመት የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱና አመጋገብና ጤናን የሚያሻሽሉ ከ200 በላይ የምርምር ስራዎች መሰራታቸው ተገለፀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው 41ኛ ዓመታዊ የምርምር እና የማህበረሰብ ተሳትፎ ግምገማ ጉባኤውን “የማህበረሰብ የመቋቋም አቅምን ማጎልበት ግብርና፤ አመጋገብ እና ጤናን ማሻሻል” በሚል መሪ ሀሳብ እያካሄደ ይገኛል፡፡

በመድረኩ ከፌደራል፣ ከክልልና ከዞን የተውጣጡ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተገኝተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዘርፎች በተለይም በግብርናው ዘርፍ ትኩረት በማድረግ የተሻሻሉ የግብርና ግብአቶች ላይ ምርምሮች መካሄዳቸው ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ባለፈም በቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ በባህል እና በቱሪዝም ዘርፉ ላይም በርካታ ምርምሮች መደረጋቸው ተነስቷል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ጉዳዮች እና የማህበረሰብ ተሳትፎ ምክትል ፕሬዚዳንት ይሳቅ ዩሱፍ (ዶ/ር)፤ በዩኒቨርሲቲው ወደ 230 የሚጠጉ ምርምሮች እንደተደረጉና 46ቱ ተጠናቅቀው ይፋ ሆነዋል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጀማል ዩሱፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲው ዘመናዊ የግብርና ስርዓትን ለመገንባት ከምስረታው ጀምሮ የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን ሲያወጣ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

የምርምር ስራዎች በህብረተሰብ ውስጥ ሰርፀው ለውጥ እንዲያመጡ ሁሉም ሴክተሮች ኃላፊነታቸውን መወጣትና ማህበረሰቡም አዳዲስ ግኝቶችን በመጠቀም ኑሮውን ማሻሻል እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

በቲያ ኑሬ

Exit mobile version