አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአረንጓዴ አሻራና የሌማት ትሩፋት መርሐ- ግብሮች በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት ለምግብ ዋስትና መሰረት መሆናቸውን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ፥ በአፋር ክልል የአረንጓዴ አሻራ ልማት በተለይም ለምግብነት ለሚውሉ የፍራፍሬ ተክሎች ላይ ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ አሻራ ልማት በብዙ መልኩ ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው ÷ በተለይም በአፋር ክልል ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
የአፋር ክልል በብዛት ይታወቅ የነበረው በአርብቶ አደርነቱ መሆኑን አስታውሰው ፥ አሁን ላይ ግን ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት እየተሻገረ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህ የሽግግር ሂደት ደግሞ በለውጡ ዓመታት በስፋት እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በክልሉ ያለውን ሰፊ መሬት በማልማት ሁሉን አቀፍ የግብርና ምርታማነትን እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የአረንጓዴ አሻራ ልማቱ የፍራፍሬ ተክሎች ላይ በማተኮር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና እንዲኖረው እየተሰራ ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራና የሌማት ትሩፋት የመሬትና የውሃ ሃብትን በአግባቡ በመጠቀም በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ ለማምረት መቻሉን ተናግረዋል፡፡