የሀገር ውስጥ ዜና

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ

By Feven Bishaw

May 28, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ከክልል እና በየደረጃው ከሚገኙ ከፍተኛ የአመራር አባላት ጋር በመሆን የክልሉን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ አስጀምረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት ÷የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በክልሉ ካስገኘው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር የህብረተሰቡን የእርስ በእርስ ትስስር በእጅጉ አጠናክሯል፡፡

የክልሉ መንግስት መርሐ ግብሩን ለማስቀጠልም አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸው፤ በክልሉ በየደረጃው ያለ አመራር ለተፈጻሚነቱ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በክልሉ በክረምት በጎ ፈቃድ ከ70 ሺህ በላይ ወጣቶችን እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማሳተፍ መታቀዱ ተመላክቷል፡፡

እንዲሁም የአቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎችን መኖሪያ ቤት እና ሌሎች ድጋፎች፣ የደም ልገሳ፣ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት እና ሌሎችንም ጨምሮ 13 ዓይነት ተግባራት በክልሉ በሁሉም ወረዳዎች እንደሚካሄዱ ታውቋል፡፡