የሀገር ውስጥ ዜና

ሀገራቸውን በውትድርና ለማገልገል የፈለጉ ወጣቶች ወደ ማሰልጠኛ ተቋም ተሸኙ

By Tamrat Bishaw

May 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን በ2016 ዓም ሁለተኛው ዙር የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምልመላ ሀገራቸውን በውትድርና ለማገልገል የፈለጉ ወጣቶች ወደ ማሰልጠኛ ተቋማት ተሸኙ።

መከላከያን የተቀላቀልነው የአባቶቻችንን አደራ ተቀብለን ሀገራችንን ለመጠበቅ ነው ሲሉም በሽኝቱ ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች ተናግረዋል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አበባው በለጠ በበኩላቸው÷ ወጣቱ ሀገሩን ከጠላት ለመጠበቅ እያሳዬ ያለው ወኔ የሚደነቅ ነው ማለታቸውን የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

በ2016 በጀት 2ኛው ዙር የሀገር መከላከያ ምልመላ በዞኑ ከሚገኙ 18 ወረዳዎችና ከተማ አሥተዳደሮች ወጣቶች በሙያቸውና በውትድርና ለማገልገል የሀገር መከላከያን እየተቀላቀሉ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ሠራዊቱን በሰው ኃይል ለማጠናከር የመመልመል እንዲሁም ወጣቱን የክብር ሙያ ባለቤት በማድረግ የሥራ ዕድል የመፍጠር ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

በተመሳሳይ የአዊ ዞን ወጣቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን ለማገልገል ወደ ማሰልጠኛ መዕከል አቅንተዋል፡፡