አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሪህ በመገጣጠሚያዎቻችን ላይ ከሚከሰቱና ከፍተኛ ህመም ሊያመጡ ከሚችሉ በሽታዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡
በሽታው በመገጣጠሚያዎች አካባቢ፣ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ በአውራ ጣታችን ላይ ድንገት በሚከሰት ከፍተኛ የሕመም ስሜት፣ በእብጠት እና በመቅላት ባህሪው ይታወቃል።
ሪህ ዩሪክ አሲድ በአጥንት መገጣጠሚያዎች ውስጥ በሚከማችበት ወቅት የሚከሰት እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በሽታው በአብዛኛው የሚጎዳው መገጣጠሚያዎችን ቢሆንም ተያያዥነት ያለው የዩሪክ አሲድ ክምችት በኩላሊት እና በሌሎች የሽንት ቱቦ ክፍሎች ውስጥ ሊፈጠሩ ይችላሉ።
በጣም ከተለመዱት የአርትራይተስ በሽታ ዓይነቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ በሽታ፤ የሕመም ስሜቱ በድንገት የሚከሰትና ብዙውን ጊዜ በሌሊት ከእንቅልፍ የሚቀሰቅስ ሲሆን በተለይ የአውራ ጣት አካባቢ ከፍተኛ የህመም ስሜት ሊፈጥር ይችላል፡፡
ሪህ አንድ ጊዜ ከጀመረ በኋላ የመከላከያ እርምጃዎችን ካልወሰድን የመመላለስ ባህሪም አለው።
የሪህ በሽታ መንሥኤዎች
ዩሪክ አሲድ የሚፈጠረው ሰውነታችን ፒዩሪን የተባለ ንጥረ-ነገርን በሚሰባብርበት ጊዜ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ፒዩሪን በተፈጥሮ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በተጨማሪም የበሬ ቀይ ሥጋ እና ጉበት ውስጥ እንደሚገኝ የሜዲካል ኒውስ ቱደይ መረጃ ያሳያል፡፡
የሪህ በሽታ ምልክቶች
ከተለመዱ የሪህ በሽታ ምልክቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ፦ • የመገጣጠሚያ ላይ ህመም፣ መቆጣት (አካባቢው ላይ ሙቀት፣ መቅላት እና ማበጥ፣ ለመንቀሳቀስ መቸገር) • በመገጣጠሚያ አካባቢ የማቃጠል ስሜት መኖር • ቁርጥማት፣ ትኩሳት እና ብርድ ብርድ ማለት የሚጠቀሱ ምልክቶች ናቸው፡፡
በርካታ የሪህ በሽታ አጋላጭ መንስዔዎች ቢኖሩም ውፍረት፣ የስኳር በሽታ፣ የኩላሊት በሽታ፣ የደም ግፊት፣ የሰውነት ቅባት (ኮሌስቴሮል) መጨመር፣ የእድሜ መግፋት፣ ማረጥና በቤተሰብ የሪህ በሽታ መኖር የበሽታው መንስዔዎች ናቸው።
በተጨማሪም ለተለያዩ ህመሞች የሚታዘዙ መድሃኒቶች፣ የዩሪክ አሲድ መጠንን የሚጨምሩ ምግቦች እና መጠጦች (ለምሳሌ ቀይ ስጋ፣ ጉበት፣ አንዳንድ የዓሳ ዝርያዎች፣ አልኮል እና ጣፋጭ/ስኳራማ የለስላሳ መጠጦች) የሪህ በሽታ ተጋላጭነትን ከፍ ያደርጋሉ።
የሪህ በሽታ መከላከያ መንገዶች
• አመጋገብን ማስተካከል (የዩሪክ ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦችን አለመመገብ ወይም ለጊዜው መቀነስ)፣ • አልኮል መጠጦችን አለመውሰድ፣ • የሰውነት ክብደት መቆጣጠር፣ • መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እና • በቀን ከሁለት እስከ ሦስት ሊትር ውሃ መጠጣት የሚመከር መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የሪህ በሽታ ሕክምና ያለው ሲሆን ህክምናውም በሁለት ዓይነት መልኩ ይሰጣል።
አንደኛው ህክምና ሪህ የሚያስከትለውን የእብጠት እና የሕመም መጠን ማስታገስ ሲሆን ሁለተኛው በደም ውስጥ የሚገኘውን የዩሪክ አሲድ መጠን በመቀነስ በበሽታው ምክንያት የሚከሰተውን ጉዳት መቀነስ ናቸው፡፡