አዲስ በባ፣ ግንቦት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተፋሰስ ልማትና አካባቢያዊ ምቹነትን ለመፍጠር የተከናወኑ ተግባራት ለዓለም አቀፍ የብዝኃ-ሕይወት ስምምነት ስኬት የላቀ አበርክቶ አላቸው ሲል የኢትዮጵያ ብዝኃ-ሕይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ስምምነቱን በአግባቡ እየተገበሩ ካሉ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን ቀዳሚ እንዳደረጋትም ነው የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፈለቀ ወልደየስ (ዶ/ር) የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ የብዝኃ-ሕይወት ጥበቃን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ፈርማ እየሰራች መሆኗን ገልጸው÷ በዋናነት ከ30 ዓመት በላይ ያስቆጠረው ዓለም አቀፍ የብዝኃ-ሕይወት ስምምነትም ዋናው ነው ብለዋል፡፡
የስምምነቱ ዓላማዎችም የብዝኃ-ሕይወት ሃብትን ማስጠበቅ፣ ዘለቄታዊ አጠቃቀምንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው ተግባር በአርአያነት የሚነሳና ለስምምነቱ ስኬት ዐሻራ የሚጥል መሆኑንም አመላክተዋል፡፡