አዲስ በባ፣ ግንቦት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ሩሲያ በህዋ ላይ የትብብር ስምምነት በመፈራረም በጋራ ጉዳዮች ላይ ፍኖተ ካርታ ለመቅረፅ ማሰባቸውን የሩሲያ የጠፈር ኤጀንሲ (ሮስኮስሞስ) ኃላፊ ዩሪ ቦሪሶቭ ገለጹ፡፡
በአዲሷ የብሪክስ አባል ሀገር ኢትዮጵያ በጣም ሰፊ ጉዳዮች መታየታቸውን ያነሱት ኃላፊው÷ የመግባቢያ ስምምነት ፈርመን በቅርብ ጊዜ ውስጥ በሁሉም ፍላጎቶች ላይ ፍኖተ ካርታ እናዘጋጃለን ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
የብሪክስ ሀገራት የጠፈር ቁጥጥር ስርዓት ላይ ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቅሰው÷ ስርዓቱም በህዋ ላይ ብዙ ዳታ መቆጣጠሪያዎች በተለያዩ ክፍሎች እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
አደገኛ ነገር ሲፈጠርም የውሳኔ አሰጣጥ ትክክለኛነትን ለማረጋገጥ ብዙ የጠፈር አካላት ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡
በመሆኑም ይህ እንደ ዓለም አቀፋዊ ስርዓት መገንባት እንደሚኖርበት በመግለፅ ከብሪክስ ምላሽ ከተገኘ የስርዓቱ የመረጃ መድረክ ሊሰፋ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
በፈረንጆቹ ሐምሌ 27 የብሪክስ አባል ሀገራት የርቀት ዳሰሳ መረጃ ልውውጥን ለማዳበር መስማማታቸውን አስታውሰዋል ሲል ኢንተር ፋክስ ዘግቧል።