አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ቡድን እና የኩባ መንግስት ንብረት የሆነው ኩባንያ አዝኩባ ጉፖ አዙካሪዬሮ በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሰረት ቡድኑ በኦሞ ስኳር ፋብሪካዎች ስራውን ጀመረ፡፡
በዚህም የኩባ ስኳር ኢንዱስትሪ ቴክኒካል ቡድን በወንጂ ሸዋ እና መተሃራ ስኳር ፋብሪካዎች ሥራውን በማጠናቀቅ በኦሞ ስኳር ፋብሪካዎች ሥራውን መጀመሩን ከኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ቡድን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የኦሞ ስኳር ፋብሪካ ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሦስት ጠቅላላ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ ማሞ ÷ቴክኒካል ቡድኑ ፋብሪካው ከፋብሪካና ከግብርና ሥራ ጋር በተያያዘ እያጋጠሙት ያሉትን ችግሮች የሚቀርፉ የማስተካከያ ሃሳቦችን ያቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ቴክኒካል ቡድኑ ያጋጠሙ ችግሮችን በተመለከተ ከፋብሪካው የዲቪዥን ዋና ስራ አስኪያጆች ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን÷ ከመጪው እሑድ ጀምሮ በኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካ ወደ ሥራ ለመግባት ማቀዱን ማወቅ ተችሏል።