የሀገር ውስጥ ዜና

ግብረ-ኃይሉ በመጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ስደተኞችን ችግር ለመቅረፍ ያደረገው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑ ተመላከተ

By Tamrat Bishaw

May 24, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሱዳን የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱ ሱዳናውያን እና የሌሎች ሀገራት ዜጎችን አያያዝ እንዲከታተል የተቋቋመው ብሔራዊ ግብረ-ኃይል እስካሁን ያደረገው የስራ እንቅስቃሴና ጥረት አበረታች መሆኑ ተመላክቷል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የሚመራው ግብረ-ኃይሉ የእስካሁን እንቅስቃሴውን አፈጻጸም ገምግሟል።

በሱዳን በተፈጠረው ቀውስ እና ወቅታዊ ሁኔታዎች መነሻ ወደ ኢትዮጵያ ሊኖር የሚችለውን የስደተኞች ፍሰት አጠቃላይ ሁኔታ ለመከታተል እና ጥገኝነት ጠያቂዎችንና ስደተኞችን በተገቢው ሁኔታ ለማስተናገድ እንዲሁም በሱዳን ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ከግጭት ቀጠናው ለማስወጣት የተሰሩ ስራዎችን ተመልክቷል።

ግብረ-ኃይሉ የተሰሩ ስራዎችን በመገምገም በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርጓል።

በመድረኩ በቀረበው ሪፖርት በሱዳን የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ከ 17 በላይ ሀገራት ዜግነት ያላቸው 128 ሺህ የሚሆኑ ፍልሰተኞች በመተማ እና ኩምሩክ ባሉ የድንበር ኬላዎች በኩል ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ተገልጿል።

ከነዚህ ውስጥ ከ47 ሺህ በላይ የሚሆኑት ተመላሽ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ከድንበር ጀምሮ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነም ተብራርቷል።

ወደ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያ እና ማዕከላት የገቡት እንደ ተጠበቀ ሆኖ ሌሎች በአዲስ አበባ እና በሌሎች ትላልቅ ከተሞች ከ15 ሺህ የሚበልጡ ሱዳናውያን ቪዛ በነፃ እየታደሰላቸው እየኖሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ይህም ሀገሪቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ አልፈው ከለላዋን ለጠየቁ ስደተኞች ያላትን ጠንካራ አጋርነት የሚያሳይ መሆኑ መመላከቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለጋሽ ሀገራት ሱዳናውያንን ጨምሮ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ያለች በመሆኑ ተገቢውን እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ የግብረ-ኃይሉ አባላት አስገንዝበዋል።