አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በታይዋን ዙሪያ የባህር እና የአየር ወታደራዊ ልምምዶችን ማድረግ መጀመሯን አስታወቀች፡፡
ለሁለት ቀናት ይቆያል የተባለው ልምምዱ የታይዋን አዲሱ ፕሬዝዳንት በሹመታቸው ወቅት የታይዋን ሉዓላዊነት አስጠብቃለሁ ሲሉ ቃል መግባታቸውን ተከትሎ የተወሰደ የማስጠንቀቂያ ልምምድ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
በታይዋን ከወር በፊት በተካሄደው ምርጫ አሸንፈው ወደ መንበረ ሰልጣን የመጡት የታይዋኑ ፕሬዚዳንት ሌይ ችንግ ቲ÷ ታይዋንን ከቻይና ፖለቲካዊ ተፅዕኖ እና ግፊት ነፃ እናደርጋታለን ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡
ታይዋን የግዛቴ አካል ናት ብላ የምታምነው ቻይና ለታይዋኑ ፕሬዚዳንት ሚስተር ሌይ ችንግ ንግግር የቃላት ምላሽ ስትሰጥ የቆየች ሲሆን ከቃላት ባለፈ የመጀመሪያውን የማስጠንቀቂያ ወታደራዊ ልምምድ በታይዋን ድንበር አቅራቢያ ማካሔድ ጀምራለች፡፡፡
የባሕር እና የአየር ወታደራዊ ልምምዱ በታይዋን ኪንመን፣ ማሱ እና ዶንጊዮን በተባሉ ደሴቶች አቅራቢያ እየተካሄደ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ቻይና በወታደራዊ ልምምዱ ምን ያህል አውሮፕላኖችን እና መርከቦች እንዳሰማራች አለመግለጿን ኒዮርክ ታይምስ አስነብቧል፡፡
ቻይና ለመጨረሻ ጊዜ በታይዋን ዙሪያ ልምምድ ያካሄደችው በፈረንጆቹ 2023 በሚያዚያ ወር ነው።