አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ተግባራዊነት እንዲፋጠን ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ 17 የአፍሪካ ሀገሮች የአህጉሪቱን አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያ በሙከራ ደረጃ ለመጀመር መስማማታቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ ንብረትነታቸው ሙሉ ለሙሉ አፍሪካዊ የሆኑ አየር መንገዶች ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው በሚያደርጉት የንግድና ገበያ ተኮር በረራ የተጣሉ ገደቦችን የሚያስቀር ነው።
የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር ዋና ጸሐፊ አብዱራሃማን በርቴ እንደገለጹት÷ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው በሚጠበቀው ልክ እንዳያድግ ከሚገድቡ ማነቆዎች መካከል በቂ የአየር ትራንስፖርት አለመኖርና የዋጋ ንረት፣ ከጥቂት አየር መንገዶች በስተቀር ምቹና ደህንነታቸው የተጠበቀ አየር መንገዶች አለመኖራቸው ነው።
ማነቆዎቹን ለመፍታት እንዲሁም በአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያን ለማፋጠን ፖሊሲ አውጪዎች በትኩረት ሊሰሩ የሚገባበት ወቅት ላይ እንገኛለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ተግባራዊ መሆን ለአቪዬሽን መስኩ እድገትና የእርስ በእርስ የገበያ ትስስርን ለማስፋት የላቀ ሚና እንደሚኖረውም ነው የገለጹት፡፡
ብዙ ሀገራት ስምምነቱን መፈረማቸው በበጎ የሚነሳ መሆኑን ጠቁመው÷ ነገር ግን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ፈጣን እርምጃ አለመወሰዱን በክፍተት ማንሳታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ይህንንም ለማፋጠን የአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀው÷ በተለይም የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን ጉዳዩን በዋናነት ይዞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ሲተገበር የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ለአህጉሪቱ ገበያ መስፋፋት የላቀ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
በአየር ትራንስፖርት የገበያ አማራጮች ለመጠቀምና ለአየር ትራንስፖርት እድገት በጋራ መስራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያ የአህጉሪቷን የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ለውድድር ክፍት ለማድረግ ከ24 አመታት በፊት በኮትዲቯር መፈረረሙ ይታወሳል።