ስፓርት

ቶኒ ክሩስ ከዩሮ 2024 በኋላ ጫማ እንደሚሰቅል አስታውቋል

By ዮሐንስ ደርበው

May 21, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሪያል ማድሪድ እና የጀርመኑ አማካኝ ቶኒ ክሩስ በቀጣይ ወር ሀገሩ ከምታስተናግደው ዩሮ 2024 መጠናቀቅ በኋላ ጫማ እንደሚሰቅል አስታውቋል፡፡

በፈረንጆቹ ጥር 4/1990 በምስራቅ ጀርመን የተወለደው ክሩስ የፕሮፌሽናል እግርኳስ ህይወቱን የጀመረው በባየር ሙኒክ ሲሆን ሶስት የቡንደስሊጋ እና ሶስት የጀርመን ጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን አንስቷል።

በፈረንጆቹ 2013 የባቫሪያው ክለብ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን 2 ለ 1 አሸንፎ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ሲያነሳ የክለቡ ቁልፍ ተጫዋች የነበረው ክሩስ፤ በተመሳሳይ ዓመት ከክለቡ ጋር የአውሮፓ ሱፐር ካፕና የዓለም ክለቦች ዋንጫን አንስቷል፡፡

በፈረንጆቹ 2014 የልጅነት ክለቡን ለቆ ወደሪያል ማድሪድ በማምራት እስካሁን በቆየባቸው ጊዜያት ከ300 በላይ ጨዋታዎችን ተጫውቶ አራት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ አራት የላሊጋ፣ አራት የአውሮፓ ሱፐር ካፕ፣ አምስት የዓለም ክለቦች ዋንጫ፣ አንድ የስፔን የንጉስ ዋንጫ እና አራት የስፔን ጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡

ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን እስካሁን 108 የተሰለፈ ሲሆን ብራዚል ባስተናገደችው የ2014 ዓለም ዋንጫ ሀገሩ ዋንጫውን ስታነሳ ክሩስ የቡድኑ ዋነኛ የመሐል ሜዳ ተጫዋች ነበር፡፡

በወቅቱ ሀገሩ ጀርመን አስተናጋጇ ብራዚልን በግማሽ ፍጻሜው በማራካኛ ስታዲየም 7 ለ 1 በሆነ አስደናቂ ውጤት ስትረታ ክሩስ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡

በአጠቃላይ እስካሁን በእግር ኳስ ህይወቱ 32 ዋንጫዎችን ማሳካት ችሏል፡፡

አሁን በማድሪድ ቤት ብቃቱን በማስመስከር ድንቅ ጊዜ ማሳለፉን የሚገልጸው ክሩስ÷ ቡድንኑ የተቀላቀለበትን ጊዜ ያመሰግናል፤ በቆይታውም በእግር ኳስ ሕይወቱ በርካታ ለውጦችን ያየበት መሆኑን ያነሳል፡፡

የሪያል ማድሪድ ፕሬዚዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ÷ ቶኒ ክሩስ በሪያል ማድሪድ ታሪክ ውስጥ ካሉ ታላላቅ ተጫዋቾች አንዱ ነው፤ ይህ ክለብ ሁል ጊዜም ቤቱ ይሆናል” ሲሉ ምስክርነታቸው ሰጥተዋል፡፡

በፈረንጆቹ የፊታችን ሰኔ 1 ቀን 2024 ሪያል ማድሪድእና ቦርሲያ ዶርትሙንድ በዌምብሌይ ስታዲየም በሚያከናውኑት የቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ጨዋታ ክሩስ ተጨማሪ ዋንጫ የሚያነሳበት ሰፊ እድል እንዳለው ይነገራል፡፡

እንዲሁም በዩሮ 2024 ጨዋታ ጀርመን ስኮትላንድን በፈረንጆቹ ሰኔ 14 በሙኒክ አሊያንዝ አሬና በውድድሩ የመክፈቻ ቀን ትገጥማች፡፡