Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከልዩ ፀረ-ሽብር ኮማንዶ አመራርና አባላት ጋር ተወያዩ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከልዩ ፀረ-ሽብር ኮማንዶ አመራርና አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡

ኮሚሽነር ጀነራሉ በልዩ ኮማንዶ ሰልጥነው በተለያዩ ግዳጆች ላይ ጀግንነት የፈፀሙና አሁን ላይም እየፈፀሙ ካሉ የልዩ ፀረ-ሽብር የኮማንዶ አመራርና አባላት ጋር በተወያዩበት ጊዜ እንደገለጹት÷ የልዩ ፀረ-ሽብር ኮማንዶ በዲስፕሊንና በትጥቅ የጎለበተና የተሰጠውን ማንኛውንም ፖሊሳዊ ተልዕኮ በብቃት የሚፈፅም ነው፡፡

የልዩ ፀረ-ሽብር ኮማንዶ በመንግስትና በህዝብ ዘንድ እንደመከታ የሚታይ፤ እንደ ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስም ትልቅ ሞራልና አቅም ሆኖ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትየጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የልዩ ፀረ-ሽብር ኮማንዶ አባላት፣ ከኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት፣ ከክልል እና ከተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የህዝብን ሰላም የሚያውኩ የሸኔ ሽብር ቡድን እና የፅንፈኛው ኃይል አመራርና አባላትን በመደምሰስ ኢትዮጵያን የማፅናትና ሰላሟን የማስፈን ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ህዝቡ ከመንግስት ጎን ሆኖ ሰላሙን የሚጠብቅበት ደረጃ ላይ መድረሱን ኮሚሽነር ጀነራሉ መግለጻቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የልዩ ፀረ-ሽብር ኮማንዶ አመራርና አባላት አቅምን ለማሳደግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ያነሱት ኮሚሽነሩ ከዘር፣ ከሀይማኖት፣ ከፖለቲካና ከሌብነት በፀዳ መልኩ አንድነታቸውን ጠብቀው ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በእኩልነት እንዲያገለግሉም አሳስበዋል።

Exit mobile version