Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጻለች፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ቃል አቀባይ ፋን ዮንግ ÷በቻይና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፣ በወቅታዊ የዓለም ሥርዓት እና በኢትዮ-ቻይና ግንኙነት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም÷ ሁለቱ ሀገራት በአካባቢ ጥበቃ እና በተባበሩት መንግስታት የዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል፡፡

በፍጥነት እየተለዋወጠ ባለው የዓለም ጂኦፖለቲካ ውስጥ ቻይና የሰላም እና መረጋጋት መርሕን አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት፡፡

ቻይና በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ሰላምና እድገት ጥብቅ ቁርኝት አላቸው ብላ ታምናለች ያሉት ቃል አቀባዩ÷ቻይና በዓለም እድገት ውስጥ ያላትን ሚና አጠናክራ ለመቀጠልና ዓለምን በምጣኔ ሃብት ለማስተሳሰር እንደቤልት ኤንድ ሮድ ያሉ ማዕቀፎችን መዘርጋቷን አንስተዋል።

በቅርቡ በቻይና የተካሄደውና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተካፈሉበት የቤልት ኤንድ ሮድ ጉባዔ የዚህ የእድገት ዓለም አቀፋዊነት እሳቤ ማሳያ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ቻይና ልክ እንደብሪክስ ያሉ ማዕቀፎችን መደገፏ የዓለምን ስርዓት በጥቂት ሀገራት ብቻ ከመመራት በብዙ ሃገራት ተሳትፎ የሚወሰን የዓለም ስርዓትን ለመለወጥ እንደምትሰራ ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በወቅታዊ የዓለም ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን÷ ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በአቅም ግንባታ እና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ እያሳየች መሆኑን አብራርተዋል።

ቻይና÷ ከአፍሪካ ጋር ያለው ግንኙነት በመከባበር ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል ብላ እንደምታምንም ቃል አቀባዩ አስገንዝበዋል፡፡

በምስክር ስናፍቅ

Exit mobile version