አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአስፈጻሚ አካላቱ በዕቅድ የተያዙ ሥራዎችና የሪፎርም አተገባበሮች ውጤታማ መሆናቸውን ተመልክተናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ለጠቅላይ ሚንስትሩ ተጠሪ የሆኑ አስፈጻሚ አካላት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀምን ዛሬ ገምግመናል ያሉት አቶ ተመስገን÷ በአስፈጻሚ አካላቱ በዕቅድ የተያዙ ሥራዎችና የሪፎርም አተገባበሮች ውጤታማ እንደሆኑ ተመልክተናል ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
በቀሪ ወራት መፈፀም ያለባቸው ተግባራትን በመለየት በዓመቱ ለማሳካት የተያዙ ትልሞችን በተሟላ መልኩ ለመፈፀም ከሥራ ኃላፊዎች ጋር መግባባት ተፈጥሯል ብለዋል።
በሪፖርቱ ከቀረቡ ጉዳዮች ውስጥ መልካም ውጤቶችን ማጠናከር፣ ያሉ ክፍተቶችን ማረምና በተያዘላቸው ጊዜ ያልተከወኑ ተግባራትን የማካካሻ ዕቅድ አውጥቶ በመሥራት ጠንካራ አፈጻጸምን ማስቀጠል እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጠናል ነው ያሉት፡፡